ድንቢጥ

ደረቷ እንደ ፀሐይ ጮራ ቦግ ያለ ነው። ዘወትር ከግቢዬ እንጨት አጥር ላይ ሆና እንዴት ዋላቹህ ለማለት ይመስል ዜማዋን በትንሹ ታሰማኛለች። “ድንቢጥዬ መጣሽ? እንደምን አደርሽ?” ስላት መልስ ባትመልስም ከአጥሬ ፈንጠር ብላ ትወርድና በጓሮዬ ከሚገኙት አትክልት መትከያዎች ላይ አረፍ ትላለች። ጉዳይዋ ስላልገባኝ ስራዬን አቁሜ ለደቂቃ ተከታተልኳት። በአጭሩ ተጣራች። ከዛፎቹ መሀል ጓደኛዋ መልስ ሰጣት። ድንገት እሱም ከአጥሬ ሰፈረ። በዛች ደቂቃ ማን ወንድ ማን ሴት ብዬ እጠይቅ ጀመር። ቆየት ብዬም መልሱን አገኘሁት። የወንዱ ደረት ከሴትዋ ይልቅ ቅላቱ የናረ ነውና።

ባልና ሚስቱ ድንቢጥ ግቢዬን ለመዱት። እኔም ያልታሰበ ተፈጥሮአዊ መዝናኛ በነፃ አገኘሁ። ደስ አለኝ። የክረምቱ ብርድ ኮሰተር ሲል ተሰማኝና ከድንቢጦቹ ጋር የነበረኝ የቅርብ እይታ ቀረ። ተረሳሳን። ክረምቱም አለፈ። ፀሐይም ግቢዬን በጮራዋ አፀዳች። «ነይ ጉድ ተመልከች። » ብለው ቤተሰቦቼ ጠሩኝ። ዓይኔን ማመን አቃተኝ። በማዳበርያ ውስጥ በስርአት የተደራጀችው የወፍ ጎጆ አምስት ድንቅ እንቁላል ታቅፋለች። ልጅ የተወለደልኝ ይመስል እልልታየን ሳቀልጠው « ኸረ ተይ ደንግጠው በዛው እንዳይቀሩ” ተባልኩኝ። ብዙም ጊዜ ሳንፈጅ አንዳንድ ፎቶ ቀጭ ቀጭ አድርገን ወደ ውሎአችን ተመለስን።

ልባችን ውስጥ ለያዝናቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለማግኘት ጉግል ላይ ሰፈርንበት። የድንቢጥ ጎጆዎች በሚስጥር የተመሸጉ ስለሆኑ ሚስጥራቸው ከወጣ ወደ ጎጆአቸው እንደማይመለሱ መሆኑን ተረዳን። ያየነውን እንዳላየ ለመምሰልም ተስማማን።

ባለፈው ቅዳሜ ከሌሊቱ አስራአንድ ሰዓት የድንቢጥ ጥሪ ቀሰቀሰኝ። በሰመመን ያዳመጥኩት ዝማሬዋ አፈላሰፈኝ። ወደ ጎጆዋ ጠላት መጥቶባት እንዳይሆን ተጨነኩኝ። ወይንስ ጥሪዋ የምስጋና ይሆን? ሰዓቱ ልክ አስራ ሁለት ሲሞላ ዝማሬዋ አቆመ። እኔም ከቅዳሴ ስወጣ የሚሰማኝ መለኮታዊ ስሜት ትዝ ብሎኝ በስመአብ አልኩኝ።

አላስችል ብሎኝ እንቁላሎችዋን ብቅ ብዬ አየሁ። አምስቱም እንዳማሩ ናቸው። በሆዴም ተጣርቼ ድንቢጥ ጎጆዋ እንድትመለስ ለመንኳት። ወደ ጎጆዋ ሄጄ ገና ያልተፈለፈሉትን ጫጩቶችዋን ስለማቀፍዋ ለማረጋገጥ ብሞክር ላስደነግጣት ስለምችል ያንን ላለማድረግ ወሰንኩኝ። ጫጬቶችዋን ለማየት ያብቃኝ ብያለሁና ድምፅዋን ለማታውቁ ከዚህ በታች የሚገኘውን አገናኝ (link) በመጫን የድንቢጥ ወፍ ዝማሬ ልጋብዛቹህ። መልካም ሰንበት።

e18ba8e18c8de189a2e18bac-e18bb5e18a95e189a2e18ca5-e18b88e18d8d.mp3

የድንቢጥ እንቁላል

(C) VN/Nightingale Jennings

Leave a Reply